ከሁሉ የላቀ ሀብት

 ቁምነገር ፒያሳ ከወርቅ ቤቶቹ ትይዩ፤ መንገዱን ተሻግሮ ከአንዱ የድንጋይ ግድግዳ ተደግፎ ወጪ ወራጁን ይቃኛል። እንደተለመደው ጠባብ አይኖቹን የባሰ አጨንቁሮ በተመስጦ ለረጅም ሰዓት ከአንዱ ጥግ ሲያፈጥ ይቆይና፤ ጥቅጥቅ ያለ ጥቁር ጢሙን እየገመደ አይኑን ወደቀጣዩ ሁነት ይመልሳል። በዚህ ሁኔታ እራሱን Busy እንደሚያደርግ ስለማውቅ፡ አጠገቡ ደርሼ እንኳን ባለማስተዋሉ አልተገረምኩም። 

ልጅ ቁምነገር አልኩ ጉሮሮዬን ጠራርጌ። ፊቱን ወደድምፄ በእርጋታ መልሶ አጤነኝና፤ ለሰላምታ እጆቹን ዘረጋ። ሀሳቡ ግን እንደሰፊ ጫማ ወደኃላ ቀርቷል።

- ወዳጄ እንዴት ነህ? ጠየኩ

- አለሁ በጤና ክብሩ ይስፋ! ያመጣን በፈቃዱ፣ ያቆየን በሀይሉ... አንተስ እንደምን ቆየህ?! አለ በፈገግታ

ሁሌም ሰላምታ ሲያቀርብ፡ ፈገግታው ቀድማ እንደ " አፒታይዘር" እንደምትቀርብ አውቃለሁ።

- አለሁ። ሁሉ ድንቅ ነው አልኩ በአንፃሩ የበረደ ፈገግታዬን እየገለብኩ።

በትከሻዬ አሻግሮ እያየ ከመቅፅበት ፊቱ ሲለዋወጥ አስተዋልኩ። ገጥሞኝ የማያውቅ አዲስ ሁነት በመሆኑ ውስጤ ተረበሸ።

በፍጥነት እኔን ካለሁበት ጥሎ፤ ወደአንዱ ወርቅ ቤት ተፈነጠረ። ምንነቱ ባይገባኝም ተከተልኩት።

ከወርቅ ቤቱ በር ላይ በሀዘን የተመታ አንድ የኔ ቢጤ በአንድ እጁ አናቱን ይዞ በሌላው ፊቱን ይጠርጋል። እንደደረስን... ሰውየውን " ና የኔ አባት ብሎ እጁን አፈፍ አርጎ ይዞት ወደውስጥ ዘለቀ።

አቤት ወንድሜ ምን ልታዘዝ?! አለ አንድ ጠየም ያለ ወጣት... ወደ ወርቅ ጌጦቹ እየጋበዘው።

ቁምነገር ቱግ አለበት! አይኖቹ ፈጠው ፤ ፀጉሩ ቆሞ መለሰለት።

ተው እንጂ?! እኔና ይህን ምስኪን ምን ለየን ጃል? እርሱ ስላጣ ይሆን ከወንድምነት የሰረዝከው? እኔን አቅርበህ ወንድሜ ያልከኝ፤ ያለኝ ብመስል ይሆን?! 

ስማ በል!... ይህ ሁሉ የያዝከው ወርቅና ብር፡ ከቁስነት ያለፈ ህይወት እንደሌለው እነግርሀለው። ምንም ያህል ቢበዛልህ፤ ተጨፍልቆ የዚህን ሰው ጥፍር ያህል እንኳን ወዝ እንደሌለው እነግርሀለው። በዚህች ዓለም ትልቁና ውዱ ሀብት ሰው ሆኖ ሳለ፤ ሰው ሰውን ትቶ፣ ወንድሙን ገፍቶ ከትቢያ ውስጥ ድንጋይ ያከብራል። አንተም ይህንኑ ነው ያሳየኸኝ። ወርቅ ብለህ የጠራኸው ድንጋይ በልጦብህ ወንድምህ ፊት ላይ ተፋህበት!? ይህን ማድረግህ ምንኛ አንተነትህን እንዳወረደው አይታይህም?! ዛሬ... መታበይህ ህሊናህን ተጭኖ፣ ሀብትህ እውነታን ከአንተ ስላራቀው፤ ህሊናህን ተክቼ ይህን እነግርሀለው። በጊዜ ላይ ያለህ ንግስና የሳሳች መሆኗ ሳይዘነጋህ አልቀረም። ዛሬ ነገህን እንደሚያንፅ፤ ትናንትህም ከዛሬ እንደሚወለድ ላስታውስህ! ዛሬ የገፋኸው ነገ ላይ አፀፋው ይጠብቅሀል። ማስተዋልህን ወደራስህ መልስ! ከዚህ ኮት ከሆነ ክብርህ ያለው... የኔ የእርሱ ሆኗል! 

ያደረገውን ቡኒ የከፋይ ኮት አውልቆ ለተገፋው የኔ ቢጤ ደረበለት፡፡ ንግግሩም ቀጠለ። 

ወርቅም ከሱ የበለጠ ከመሰለህ...ደግመህ እራስህን ጠይቅ። ይህን ብሎ ያጠለቀውን የወርቅ ሰዓት ፈቶ አደረገለት።

እንግዲህ ወንድሜ! እስኪ አሁን ከተቻለህ ደፍረህ ምራቅህን አልብሰው፡፡ አስተሳሰብህ ለልብስና ለጌጥ የበለጠ ክብር አለውና ይህን ማረግ ይከብድሀል! ልብሱና ወርቁ የምራቄ ጢቅታ አይገባቸውም ብለህ ይሆን ዝም የምትል?!

ጠይሙ ወጣት በድንጋጤ ተውጦ ዝምታን መርጧል። የኔ ቢጤው ባለ-ሀገር በደረሰው ፍቅር ልቡ ተነክቶ መንታ መንታውን ያወርደዋል።

ለሂሳብ ስራ የተሰየመች አንዲት ጠና ያለች ሴት ጥጓን ይዛ የተፈጠረውን ባለማመን አይኗ ፈጦ ቆማለች። የቁምነገር እውነታ ሁላችንንም ሳይነካ አልቀረም። ቤቱ ሁሉ በፀጥታ ተውጧል።

እንግዲህ እውነታዬን አፍኜ መታመምን አልፈቅድም። ከራሱ ጋር እየተጋጨ የሚታመም ወንድሜ ህመሙ ያመኛልና፤ የተገፋውም በዳዩም በቤቴ ቢገኙ፡ ወንድምነታቸው " በአጣ ነጣ" እና " በአገኘ አበጠ" ተከፍሎ ልዩነቱ ባይታየኝ ነው እንዲህ መናገሬ። ጓዳችን ሰላሙ እንዲመለስ፡ መተሳሰባችን የግድ ነውና መናገሬን እመርጣለሁ። እንግዲህ ምን ትላላችሁ?! ብሎ ጥያቀውን ለቤቱ መራው። 

ጠይሙ ወጣት ያበጠ ልቡ በእውነቱ ቃል ተሸርሽሮ በዕድሜ ከፍ ካለው ወንድሙ እግር ስር ጣለው። ወድቆም ይቅርታን ጠየቀ።

ተበዳይ በሀዘኔታ ከወደቀበት አንስቶ በይቅር ባይነት ሰላሙን ሰጠው። በወርቅ ቤቱ ልቅሶ በዛ። የደስታ ልቅሶ! የደስታ ድባብ ፀለለ። ከወርቅ ቤቱ ውስጥ የተደረደሩ ጌጦኝ እራሱ ቦታቸውን ያወቁ ይመስል ደብዘዝ ብለው ታዩኝ። 

እውነት ነው! ሰው ነው የዓለም ትልቁ ሀብት። ሌላው ሁሉ ከንቱ ነው። ሌላው ሁሉ ኃላ ነው።