ትላንት - ዛሬ - ነገ

ከየትና እንዴት? ከቶስ በምን ፍጥነት ተችሎት እነዚያን የበሰሉ ቃላት ያለግድፈት በመሳጭ ቃና ሾርቦ እንደሚያቀርባቸው ሁሌም ይደንቀኛል። የተፃፈ ወረቀት ጢሙ ውስጥ የደበቀ ይመስል ጥቁር ችምችም ያለ ጢሙን ዳበስ ዳሰስ ሲያደርግ ቆይቶ በስሱ ወደኃላ ለጠጥ ይላል። ቀጥሎም አይኑን ከተደራሲው ገፅታ ላይ ተክሎ በእርጋታ ቃላትን ማዝነብ ይጀምራል። ዝናቡ ግን ከቶ የግፊታምነትና የችኩልነት መልክ የለውም። ይልቁንስ በእርጋታና በትዕግስት አለትን እንደምትበላ ጠብታ፤ በረጋ ምት ወደውስጥ ዘልቆ የመግባት ብርታት አለው። የቃላቱ ክብደት የሀሳቡን ድርሰት ሳይጋፉ፤ የሀሳቡም ይዘት በቃላቱ ውበት ሳይከለል፡ መድረስ ካለባቸው መዳረሻ ይሰርጋሉ። አዕምሮው ይፈትሻሉ። ምልከታን ይሞርዳሉ። ከልብ ምት ተዋህደው ላይጎረብጡ ይሰካሉ።

በአንድ ወቅት " አንተ ግን ምንድነህ?" ብዬ ላነሳሁበት ጥያቄ ምላሹ አይረሳኝም። 

በተለመደው እርጋታው ታጅቦ ከቆየ በኋላ፡ " በዕውነት እኔ ሰው ነኝ! በአምሳሉ የተቀረፅኩ ለታላቅነት የታነፅኩ ቤቱ ነኝ። በአንፃሩ ጥያቄህ ስራህ ምንድነው ከሆነ ሊገለጡልኝ ከወደዱ ጥበቦች መሀል ልገለጥበት የፈቀድኩት፡ የውስጥ ሰላሜንም ያልተጋፋ የተከበረ ሙያ አለ። ሀኪም ነኝ! ሀኪምነቴ ግን የሰውን ብልት ለመቁጠር፤ ለመቀነስ አሊያም ስለመጨመር አይደለም። ፈዋሽነቴ የጠነከረልኝ በአስተሳሰብ ላይ ነው። ሀኪም ነኝ! የአዕምሮ በሽታን የምፍቅ የአስተሳሰብ ጉድፈትን ለማንፃት የምተጋ ሀኪም። " ነበር ያለኝ ከሞቀ ፈገግታ ጋር። እኔም ከርሱ ጋር ተጫውቼ እራሴን አስፍቼ፤ የአስተሳሰብ ድሪቶዬን ጥዬ፤ ማንነቴን ፈልፍዬ ያልሄድኩበት ቀን ትዝ አይለኝም።

ዛሬም እንደወትሮአችን... ወር በገባ በመጀመሪያው ቅዳሜ፡ እንደአግባባችን ከአንድ ካፌ በረንዳ ተቀምጠናል። እኔ ማክያቶ አዝዣለሁ። እርሱ ደግሞ ቀዝቃዛ ቶኒክ ከሎሚ ጋር ይዟል። የተለመዱ የተለምዶ ጥያቄዎችን ተጠያይቀን ወደ ሞቀ ጨዋታ ከዘለልን ግማሽ ሰዓት አልፎናል።

በጨዋታ መሀል...

-ስለ ነገህ ግን ምን ታስባለህ?- አልኩት።

ከአስፋልቱ ማዶ ለቅፅበት አየና ፊቱን ወደ እኔ መልሶ ፈገግ አለ። እጁ የጢሙን ላይ ላይ ትዳብሳለች። ወደኀላ እንደልማዱ ለጠጥ ብሎ እንዲህ አለ...

<<በዕውነቱ ነገዬ በህሊናዬ ልትመላለስ አልተቃኘችም። አዕምሮዬም ቢሆን ነገን ሲያስብ ከመልሱ ይልቅ ጥያቄው ይበዛል። ነገ በፈጣሪ ጥበብ፤ በጊዜ ቀለም ትነደፍ እንደሁ ግን አውቃለሁ። የዕውቀቴ አለም ዛሬዬ ነገ እንደሆነች ይነግረኛል። ልቤም በነገ ሳይሆን ስለዛሬ እንዲበረታ አስተምሬዋለሁ።

ዛሬ የትላንት ነገ ነው! ነገም ለዛሬ ነው ነገነቱ! የቀንህ ብርሀን መሀል ላይ ነው። ከጠዋት ብትቀድምም ድቅድቅ ጨለማ፤ ወደአመሻሹ ብትዘልም የደከመ ብርሀን እንጂ ከቶ የተትረፈረፈውን አታገኝም! >>

የቁምነገር ቃላት መረጣና የተምሳሌት ብቃት አፍን ከፍቶ ከማዳመጥ ውጪ ነቅነቅም ለማለት እድል አይሰጥም። እኔም አፌን ከፍቼ ማድመጤን ቀጥያለሁ!

<< እንግዲህ አስተውል! ስለምን ይሆን ዛሬን ከመሬት ተዘርፍጠን ነገ እንዲያነሳን ምንጠብቅ? ትላንት ላይ ቆመን ዛሬን ነገ ብለን ጠርተነዋል። ተስፋችንስ በሱ ላይ አልነበረም? ደስታችንንስ ቢሆን በይደርሳል እነገ ጎሬ አልወሸቅነውም? 

ታዲያ ነገ ባለበት ዛሬ እንዴት ተደርጎ ይኖራል? ሁላችን የጊዜ ትርጉሙ ጠሞብናል ልበል? 

ነገና ትላንት እኮ በዛሬ ውስጥ ነው። ጊዜ ባርያነቱ ለዛሬ ፤ እኛስ ንግስናችን በዛሬ ላይ አይደለም እንዴ? ንጉስ ያለሀገሩ ገብቶ ህግ ቢያወጣ ማን ሊታዘዘው ይፈቅዳል? 

ነገን የተሻለ ለማድረግ ዛሬ ምን አደረግክ ነው ጥያቄው።

ስለዚህ ዛሬ ላይ በቅጡ፣ በቅንነት፣ በብቃት ፣ በፍቅር ንገስባት። የተባረከ ነገን እና ሰላማዊ ትላንት ትፈጥርልሀለች።

አልያ ግን ላልተገባን ተሰጥተን፤ በምን ነበር አለንጋ ሰንበር እያበጀን፤ ነገንም በሰቆቃ እየጠበቅን ጊዜአችንን ማምከን ነው ትርፉ።>>

ይህን ብሎ አሻግሮ ማዶውን መቃኘት ያዘ። የሚገርመኝ ደግሞ የፈለገ የጠጠረ ጥበብ ቢናገር፤ ምንም ያህል ወቀሳን ቢሰነዝር... ሲያወራ እራሱን አካቶ "እኛ" እያለ ከተወቃሹና ከአላዋቂው ጋር ሲደበል አድማጩን ከብቸኝነት ጭንቀት ነጥሎ የተወራው ሀሳብ ላይ እንዲያተኩር ማድረጉ ነው። እኔም እንዲሁ በነፃነት በጥያቄ አለም ስለዛሬዬ እያውጠነጠንኩ የበረደ ማኪያቶዬን ተጎነጨሁ።