"ሰው ነበር"

ሞትኩ አሉ! የቀብሬ ስርዓት በየወጉ ሲሰናዳ፤ ከአየር ላይ ተንሳፍፌ፡ በድኔን ካለበት ጥዬ ሁነቱን እታዘባለሁ። ዘመድ አዝማዱ ሁሉ ልቡ ተሰብሮ መልኩ ሁሉ እርቆታል። ሀዘኑ የበረታበት ደግሞ ከአይኑ ኩሬ ግለትና ሀዘን ያዘለውን እንባ ከሳግ ቀላቅሎ እንደጉድ ያወርደዋል።ግማሹ ድንኳን ይጥላል። ሌላው ንፍሮ ይቀቅላል። ይህን ሁሉ ስታዘብ ቆይቼ ደግሞ ማረፊያዬን ላይ... መንፈሴን ወደተማሰው አፈር አሻገርኩት። 
 መሬቷ ታሳዝናለች። በሰዎች ትዕዛዝ መሰረት... በኔው ሰውኛ ቁመት ልክ አፏን ከፍታ ቀርታለች። እኔነቴን አግኝታ፤ አላምጣኝ እስክትረካ፤ ከሆዷ እስክወሀዳት አፏን በእጅጉ ከፍታ ሆዷን ታስመርቃለች። ምድሪቷን ታዝቤ በወጉ እንኳን ሳልጨርስ ፤ የመቃብር ደንጊያዬ በህሊናዬ ዘለለ። ከነፍኩ... በረርኩ...
 ድንጋይ ቆርቋሪው ጢማም ከሚሰራበት ደረስኩኝ። አንዲት ቁራጭ ስንጥር ቢጤ ከአፉ ውስጥ ወሽቆ በምላሱ ያለፋል። እየቆየ እየቆየ በምራቁ ጢቅታ መሬቲቷን ያርሳል። ከድንጋይ ፊት ተደንቅሮ እራሱን ለስራ ያሰናዳል። መፈልፈያውን ስቦ፤ የወየበ ሸሚዙን እስከ ክርኑ ሰብስቦ... በአንዲት ወረቀት ላይ የተፃፉትን የቃላት ስብስብ አጨንቁሮ ያነባል። ከጆሮ ግንዱ ተለጥፌ አብሬው አነበብኩ። ለወዲያኛው ዓለም መግቢያ ትኬት ይመስል...በህዝባር የታጀቡ( ዶ/ር ኘ/ር) የበዙ ማዕረጎች ወረቀቷን ሞልተዋታል። ትዝብት ቁጥር ሁለት፦ ነበር ላይጠቅም ሰው ለነበር ሲታገል ያስቃል። ያነበብኩት አልጣመኝም። እንደ ነፋስ ነፍሼ ወረቀቷን ከእጁ ቀምቼ ሰወርኳት። 

 ያነበበውን ለማስታወስ ሲታገል ከጆሮው ተጠግቼ ሀሳቡን በረዝኩበት። 
<< ሰው ነበር! ሰው ነበር! ሰው ነበር... >>
ያቃጨለበት ካሰበው ተጋጭቶ፤ ድምፄ ሀሳቡ ሆኖ በድንጋዩ ላይ ፀና። 
መታወስ ሰው በመሆን ነው። ሰው ነበር መባሉ በልጦብኝ ያን ሁሉ የሰውኛ ማዕረግ አራግፌ ጣልኳቸው። ደስታዬ በዝቶ ዘለልኩ። የራሴን የራስ ደንግያ ስንኞች ለራሴ እየደጋገምኩ ከነፍኩኝ። ፊት የሌለው ፊቴ በርቶ ይህንን አነበነብኩ። 
<<ወንድም ነበር፣ ጓደኛ ነበር፣ ፣ ባል ነበር፣ አባት ነበር፣ መልካም ነበር፣ ሰው ነበር! ሰው ነበር! ሰው ነበር! >> 

"ሰው ነበር " ውስጥ ሙገሳም ወቀሳም አለና፤ ዘመን አይሽሬ እውነትነት አለው።